የሀገር ውስጥ ዜና

ከ4 ሺህ በላይ ሐሰተኛ ዶላር ይዞ የተገኘው ተከሳሽ በጽኑ እስራት ተቀጣ

By amele Demisew

October 08, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ4 ሺህ በላይ ሐሰተኛ የአሜሪካ ዶላር ይዞ የተገኘው ተከሳሽ በዘጠኝ ዓመት ጽኑ እስራት መቀጣቱን ፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ተከሳሽ ተስፋዬ ፀጋዬ ሕዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም ከጠዋቱ 1 ሠዓት ገደማ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ሰዓሊተ ምኅረት አካባቢ ሞተር ሳይክል እያሽከረከረ ሳለ በአካባቢው ከሚገኝ ዐደባባይ ግንብ ጋር ተጋጭቶ ጉዳት እንደደረሰበት እና በወቅቱ÷ የዐቃቤ ሕግ ምስክር የሆነው ፖሊስ ደርሶ መታወቂያ ሲጠይቀው 4 ሺህ 550 ሐሰተኛ የአሜሪካ ዶላር ይዞ መገኘቱ ተገልጿል፡፡

ይህን ተከትሎም በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 359 መሰረት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት በፈፀመው ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን ይዞ መገኘት ወንጀል ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር አቅርቦ ማሰማቱን ፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

በዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉም ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ በዘተኝ ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡