አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ)ግሎባልፈንድ በኢትዮጵያ ቲቢ ላይ ትርጉም ያለው ስራ እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ከግሎባል ፈንድ ካንትሪ ቡድን ጋር በግሎባል ፈንድ የ6ኛ ዙር አፈጻጸም እና የ7ኛ ዙር የመጀመሪያው ሩብ አመት አጀማመር ግምገማዊ ውይይት አድርገዋል።
ይህ ግራንት ለወባ፣ ለኤች አይ ቪ፤ ለቲቢ መከላከል እና መቆጣጠር እንዲሁም ለጤና ስርአት የማጠናከር ስራዎችን የሚረዳ ነዉ።
የሶስት አመት የ6ኛ ዙር ግራንት ባለፈዉ ሰኔ መጠናቀቅን ተከትሎ አዲሱ የ7ኛ ዙር ግራንት ሃምሌ 2016ዓ.ም መጀመሩን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ዶክተር መቅደስ ዳባ በውይይቱ ወቅት ÷ የ6ኛ ዙር ፈንድ በጣም ጥሩ አፈጻጸም እንደነበረው አስታውሰው ለሌሎች ሀገራት አርአያ ሊሆን የሚችሉ ስራዎች የተሠሩበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አዲሱ የግሎባልፈንድ 7ኛ ዙር ግራንት ገንዘብም ግዜዉን ጠብቆ ከግሎባል ፈንድ ወደ ኢትዮጵያ የተላለፈ ሲሆን÷ የጤና ሚኒስቴር ገንዘቡን ወደ ክልሎች መተላለፉንና ወደ ስራ መገባቱንም ገልጸዋል።
ካለፈው አፈጻጸም ትምህርት በመውሰድ በ 7ኛ ዙር ግራንት የበለጠ አፈጻጸም እንዲኖር በትኩረት እንዲሚሰራ የገለጹት ዶክተር መቅደስ ለተደረገው ድጋፍ ለግሎባል ፈንድ ምስጋና አቅርበዋል።
የግሎባል ፈንድ የኢትዮጵያ ፖርትፎሊዮ ማናጀር ዶክተር ጆን ሳካቨሪሊያዝ በበኩላቸው÷ በግሎባንድ ፈንድ 6ኛ ዙር ግራንት አፈጻጸም መደሰታቸውን ገልፀው የ7ኛ ዙር ግራንት አሰራሩም በዚሁ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የወባ በሽታ ቁጥር መጨመር ከግንዛቤ በማስገባት እንደሚሰራ ጠቁመው ቲቢ ላይም ትርጉም ያለው ስራ እንደሚሠራ ገልጸዋል።