Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ተመድ ለኢትዮጵያ ልማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የኢትዮጵያን የልማት ቀዳሚ ጉዳዮች ለመደገፍ እና የዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራን ለማሳለጥ በትኩረት እንደሚሠራ አረጋገጠ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በትናንትናው ዕለት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው ለተሰየሙት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የእንኳን ደስ አለዎት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

በመልዕክቱም÷ ተመድ እና ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የሀገሪቱን ልማት ማጎልበት በሚችሉ ጉዳዮች ላይ በትብብር በመሥራት የረጅም ጊዜ አጋር መሆናቸውን አንስቷል፡፡

በዚህም ተመድ የሀገሪቱን የልማት ቀዳሚ ጉዳዮች ለመደገፍ እና የዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራን ለማሳለጥ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን ነው ያረጋገጠው፡፡

ለዚህ ደግሞ ከአዲሱ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ጋር በጠናክራ ትብብርና ቅርበት እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል የቀድሞዋ ፕሬዚዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ በነበራቸው ቀናኢ ትብብርና ቁርጠኝነት ለጋራ ግቦች እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን በመግለጽ ምሥጋና አቅርቧል፡፡

በተመሳሳይ የተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይና የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር) በበኩላቸው ለፕሬዚዳንቱ ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ቅድሚያ ሰጥታ በምታከናውናቸው ተግባራት ተመድ አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል አረጋግጠዋል።

Exit mobile version