የሀገር ውስጥ ዜና

በሎጂስቲክስ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

By amele Demisew

October 08, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሎጂስቲክስ ዘርፍ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል።

“የሎጂስቲክስ ትራንስፎርሜሽን ለዘላቂ እድገትና ብልጽግና “በሚል መሪ ሃሳብ በፈረንጆቹ የ2023 የዘርፉ አፈጻጸም የእውቅና መድረክ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ፣የብሄራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፣ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እና የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን አመራሮች ተገኝተዋል።

አለሙ ስሜ ( ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የሎጂስቲክስ ዘርፉን አቅም እና አፈጻጸም ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በተለይም የዘርፋን አሰራሮችን በማዘመን፣ መሠረተ ልማት ማሟላት፣ብቁ የሰው ሃይል ማፍራትና ኤክስፖርት ሎጂስቲክስን ከማስፋት አንጻር ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።

በዓለም ባንክ መመዘኛ መስፈርት መሠረት በፈረንጆቹ 2023 የኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ደረጃ በገልተኛ አካል ተፈትሾ መሻሻሎች ማሳየቱንም ተናግረዋል።

አብዱልበር ሸምሱ ( ኢ/ር)፥ በበኩላቸው የኢትዮጵያ አለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ በየዓመቱ ከፍተኛ እድገት እያሳየ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ለአብነትም በ2016 ዓ.ም የገቢና ወጪ ንግድ እቃ እንቅስቃሴ ከ15 ነጥብ 6 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ መድረሱን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ የሎጂስቲክስ ዘርፉ አፈጻጸም ኢንዴክስ ከነበረበት 2 ነጥብ 53 ወደ 2 ነጥብ 94 ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።

በትዕግስት አስማማው