የሀገር ውስጥ ዜና

በሊባኖስ የሚገኙ ዜጎች ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ እየሠራሁ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

By ዮሐንስ ደርበው

October 08, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን በትኩረት እየሠራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ÷ በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የቴክኒክ ኮሚቴ አቋቁሞ በልዩ ትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ከአሁን በፊት በተለያዩ ሀገራት ለችግር የተዳረጉ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ቀዳሚ ትኩረቱን በሊባኖስ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በማድረግ እየሠራ መሆኑንም ነው የገለጸው፡፡

ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ቤይሩት የሚገኘው ቆንስላ ጀኔራል ጽሕፈት ቤት የዜጎችን ምዝገባ እና ክትትል በተሻለ ፍጥነት እንዲያካሂድ አስተባባሪ አመራር ወደ ሊባኖስ ተልኮ ሥራ መጀመሩን ገልጿል፡፡

ቆንስላ ጀኔራል ጽሕፈት ቤቱ ያለበትን ሀገር ቋንቋ የሚችሉ ተጨማሪ ሠራተኞችን በመቅጠር እየሠራ መሆኑ እና በአሁኑ ወቅትም በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በአካል እና በዲጂታል አማራጮች ምዝገባ እያከናወነ ይገኛል ተብሏል፡፡

በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በቆንስላ ጀኔራል ጽሕፈት ቤቱ በተጠቀሰው አድራሻ እና በዲጂታል መመዝገቢያ እንዲመዘገቡ ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ሚኒስቴሩ ዜጎች አንጻራዊ ደኀንነት ወደ አለበት የሊባኖስ አካባቢ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ሕጻናት እና ሴቶችም ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ሁሉንም አማራጮች ለመጠቀም ከተለያዩ አካላት ጋር ጥረት እያደረገ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሁን ላይ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲው ቅድሚያ በሊባኖስ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሰጥቶ ደኀንነታቸው ችግር ላይ እንዳይወድቅ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡