አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢሲ) በሐረሪ ክልል የመንገድ መሰረተ ልማት ተደራሽነትን ለማሳደግ 1 ቢሊየን ብር የሚጠጋ በጀት ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ቢሮ ገለፀ።
የቢሮው ሃላፊ አቶ ኢብሳ መሀመድ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ የመንገድ መሰረተ ልማትን ለማስፋት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው።
በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙት የመንገድ ልማት ስራዎችም ፍትሀዊነት እንዲሁም ጥራት እና ፍጥነት መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለመንገድ መሰረተ ልማት ስራው 1 ቢሊየን ብር የሚጠጋ በጀት መመደቡን ጠቅሰው፤ የገጠር ወረዳዎችን የመንገድ ተደራሽነት 88 በመቶ ለማድረስ በዕቅድ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በከተማ 10 ነጥብ 51 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ መሰረተ ልማት ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም በከተማ እና ገጠር 320 ኪሎ ሜትር ነባር የጠጠር መንገድ፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ እና የጥርጊያ መንገዶችን ጥገና ለማካሄድ እየተሰራ መሆኑን መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።