Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሊባኖስ የነበሩ 51 ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢሲ) በሊባኖስ ይኖሩ የነበሩ 51 ኢትዮጵያዊያን በሁለት በረራዎች በዛሬው ዕለት ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡

በሊባኖስ የሚኖሩ ወገኖችን በቀጣናው ባለው አለመረጋጋት ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ እየተደረገ ነው።

በዚሁ መሠረት ዛሬ 51 ኢትዮጵያዊያን ከሊባኖስ ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሲሆን÷ በዚሁ ወቅት የብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማርያም (ዶ/ር)፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

በዚሁ ወቅት የሥራ ኃላፊዎቹ ባደረጉት ንግግር በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ደኅነታቸው ተጠብቆ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በሊባኖስ የሚኖሩ ወገኖችም በቀጣናው በሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል ጽሕፈት ቤቶች በመመዝገብ ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚችሉበትን ዕድል እንዲጠቀሙ አስገንዝበዋል፡፡

ተመላሽ ዜጎች በበኩላቸው በአስከፊ ችግር ውስጥ እንደነበሩ በመግለጽና ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ላደረገላቸው ትብብር አመስግነው÷ ሌሎች በሊባኖስ የሚኖሩ ወገኖች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ድጋፉ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በይስማው አደራው

Exit mobile version