የሀገር ውስጥ ዜና

ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምን ማስፈንና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴ

By Feven Bishaw

October 07, 2024

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምን ማስፈን እና የህግ የበላነትን ማረጋገጥ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው ሲሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀስላሴ ተናገሩ፡፡

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።

በዚሁ ወቅት ፕሬዚዳንት ታዬ ለሁለቱ የፌዴራል መንግሥት ምክር ቤቶች ዓመታዊ ሥራቸውን መጀመራቸውን በማብሰር የፌዴራል መንግሥቱን ዓመታዊ ዕቅድ አቅርበዋል፡፡

በንግግራቸውም ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር ሃይልን በብቸኝነት መጠቀም መብት የመንግስት ተቋማት ብቻ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡

ዓመቱን የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነት አፈፃፀም የሚሻሻልበት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለምንገነባው ዘላቂ ሰላም ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

ይህም በህብረብሔራዊነት ያጌጠች ኢትዮጵያን የማፅናትን ምዕራፍ እዉን ያደርጋል፤ ሀገራዊ ምሰሶዎችን ያፀናል ሲሉም ገልጸዋል።

ዛሬም በድጋሚ መቀራረብ፣ መነጋገር፣ መከራከረ፣ መግባባት እንዲሁም አብሮ መቆም የመጨረሻ ግባችን ሊሆን ይገባል በማለት ጠቅሰው፤ ለዚህ ሁሉ ግን የመተማመን ዋጋ ላቅ ያለ መሆንን መረዳት እንደሚያስፈልግም ነው ያስረዱት፡፡

በእኛ በኩል ለመጪው ትውልድ የምሰጠው ስጦታ ይህ ሊሆን ይገባል፤ በሁሉም ረገድ ሰላምን የማምጣትና የማረጋገጥ ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም ዋንኛው በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኩል የሚሰራው ስራ መሆኑን አንስተው፤ ኮሚሽኑ የዝግጅት ምዕራፍ ተግባራት አጠናቅቆ በ2016 ዓ.ም ወደ ምክክር ተግባርት መሸጋገሩን አስታውሰዋል፡፡

በዚህም አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችንና ጥያቄዎችን ማሰባሰብ መቻሉን ገልፀው፤ ኮሚሽኑ እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳች ላይ አካታች ምክክሮችን በማድረግ የተሻለ ሀገራዊ መግባባት ለመገንባ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በሂደትም የመተማመን እና ተቀራርቦ የመስራት ባህልን ለማጎልበት መንገድ ይከፍታል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱን ለማሳለጥ ኮሚሽኑ የተጣለበትን ተስፋና የታለመለትን አላማ እውን እንዲያደርግ የሁሉም ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል።

በመንግስት በኩል አሁንም ቢሆን የሰላም በሮች እንደተከፈቱ መሆናቸውን ገልጸው፤ በተናጠልም ይሁን በጋራ መንግስት በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገር ሁልጊዜ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

ከዚህ ውጪ የሃይል አማራጭን በመጠቀም ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለሟሟላት የሚደረጉ ማናቸውንም እኩይ ተግባራት መንግስት በልበ ሰፊነት ሚያልፍበት እድል እጅግ ጠባብ ነው ብለዋል፡፡

በልበ ሰፊነት ብዙ ጊዜ ተሰጥቷል፤ የህዝቡን የዘመናት አብሮነት እሴት የሚያላሉ ተግባር በሚፈፅሙ ግለሰቦችና ቡድኖች፣ ህዝብን ከህዝብ በሚያጋጩ አካላት ላይ መንግስት እርምጃ ይወስዳል ነው ያሉት፡፡

በፌቨን ቢሻው