በ2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ 8 ነጥብ 4 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ይሰራል – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ 8 ነጥብ 4 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ጥረት ይደረጋል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ተናገሩ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
ፕሬዚዳንት ታዬ በአዲሱ በጀት ዓመት በመንግሥት የሥራ አቅጣጫዎች ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በ2107 ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ዘርፍ ለመገንባት የመስኖ ሜካናይዜሽን ስራዎች እንዲጠናከሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ከግብዓት አቅርቦት ጋር በተያያዘ በተለይ የውጭ ምንዛሬ እና የብድር ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ ተግባራዊ የተደረገው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማነት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት፡፡
በዚህም በበጀት ዓመቱ በኢትዮጵያ 8 ነጥብ 4 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ጥረት ይደረጋል ሲሉ ገልጸዋል።
ጠንካራ ተቋማዊ አቅም ለመፍጠር፣ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ ከባቢያዊ ሁኔታን ለማሻሻልና አገልግሎት ዘርፉን ዲጂታላይዝ ለማድረግ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
ታክስና ታክስ ያልሆኑ ገቢዎችን በማሻሻል አጠቃላይ የመንግስትን ገቢ 1 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር ለማድረስ እንደሚሰራ ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት፡፡
ጥብቅ የሆነ የፊስካል እና የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማጎልበት እንደሚሰራም አስገንዝበው፤ ከአቅርቦት አንጻር ያሉትን ተግዳሮቶች በመፍታትና የገበያ ሰንሰለት መቆራረጦችን በመቅረፍ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ጥረት እንደሚደረግም አንስተዋል፡፡
የወጪ ንግድን ለማሻሻል አዳዲስ ምርቶችን እሴት ጨምሮ በመላክ ከዘርፉ ከ5 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት በትኩረትና በትብብር እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ