የሀገር ውስጥ ዜና

መንግስት በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ተከታታይነት ያለው እድገት ማስመዝገብ ችሏል – ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ

By Shambel Mihret

October 07, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ተከታታይነት ያለው እድገት በሁሉም ዘርፎች ማስመዝገብ መቻሉን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ ላይ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ንግግር አድርገዋል፡፡

በንግግቻቸውም÷መንግስት በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ተከታታይነት ያለው እድገት በሁሉም ዘርፎች ማስመዝገብ መቻሉን አንስተዋል፡፡

በተለያዩ ውጣውረዶች እያለፍንም ቢሆን በ2016 ዓ.ም 8 ነጥብ 1 በመቶ ጥቅል ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ችለናል ብለዋል፡፡

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ስጋቶችንና ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን አመላካች ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ባለፈው በጀት ዓመት 13 ነጥብ 8 በመቶ እድገት ማሳየቱን በመግለጽ በዚህም 3 ነጥብ 9 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የኢንቨስትመንት ፍሰት ተመዝቧል ብለዋል፡፡

ኢኮኖሚያችን አዲስ የታሪክ እጥፋት ላይ ነው ያሉት አምባሳደሩ÷ኢኮኖሚያችን እውንና ገቢር እንዲሁም ገበያ መር እየሆነ በዓለም ተወዳዳሪ እንዲሆን መሰረቱን ከነጠላ ዘርፍ እድገት ወደ ብዙሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ እየተሸጋገረ ነው ብለዋል፡፡

በግብርና መስክ ባለፈው አመት 6 ነጥብ 9 በመቶ እድገት በመመዝገቡ የህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መሰረት እየጣለ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በሌማት ቱሩፋት ንቅናቄ በሁሉም ክልሎች ከፍተኛ ምርት መገኘቱን ጠቅሰው÷ በእንስሳትና በእንስሳት ተዋጽዖ፣ በማርና በዓሳ ምርቶች አበረታች ለውጥ መጥቷል ብለዋል፡፡

መንግስት ለተፈጥሮ ጥበቃና ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት መስጠቱን አስታውሰው÷ በአረንጓዴ አሻራ ባለፉት ስድስት ዓመታት 40 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ተችሏብም ነው ያሉት፡፡

በኢንዱስትሪው መስክ 9 ነጥብ 2 በመቶ እድገት ተመዝግቧል ያሉት አምባሳደሩ÷ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ምርታማነት እድገት 59 በመቶ ደርሷል ብለዋል፡፡

የሁሉም ባንኮች ሀብት 2 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር መድረሱን፣ የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች 39 ነጥብ 6 ሚሊየን መድረሱን እንዲሁም የመንገድ ሽፋን 169 ሺህ 600 መድረሱን ጠቁመዋል፡፡

የንጹህ ውሃ ተጠቃሚዎች ቁጥር 74 ነጥብ 8 ሚሊየን መድረሱንና የአባይ ግድብ አጠቃላይ ግንባታ 96 ነጥብ 7 በመቶ በላይ መጠናቀቁንም በንግግራቸው አንስተዋል፡፡

በየሻምበል ምህረት