አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ነው፡፡
በዚህም የፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ የሥራ ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሰይመዋል፡፡
አምባሳደር ታዬ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው ከመሰየማየቸው በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬም በምክር ቤቶቹ ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ የፈጸሙ ሲሆን÷ ከቀድሞዋ ፕሬዚዳንት ሣለወርቅ ዘውዴም የሥራ እርክክብ አድርገዋል፡፡
በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ የተወለዱት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ÷ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት እንዲሁም የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከእንግሊዙ ላንክስተር ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና በስትራቴጂ ጥናት አግኝተዋል።
እንዲሁም አጫጭር የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ፖለቲካል ሳይንስ ሥልጠናዎችን እና ኮርሶችን በተለያዩ ሀገራት ተከታትለዋል፡፡
የሥራ ሕይወታቸውን በተመለከተም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ መምሪያ የሥራ ክፍል፣ የምዕራብ አውሮፓ ዋና ክፍል ኃላፊ፣ የኢንፎርሜሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር፣ በስቶክሆልም የኢፌዲሪ ኤምባሲ አማካሪ፣ በዋሽንግተን የኢፌዲሪ ኤምባሲ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል።
እንዲሁም በ1998ዓ.ም በሎሳንጀለስ ቆንስላ ጀነራል ባለሙሉሥልጣን አምባሳደርነት መሾማቸው እና በሎስአንጀለስ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት ማዕረግ የቆንስላ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡
በአውሮፓ እና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል እና በ2008 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴዔታ በመሆንም አገልግለዋል፡፡
በሌላ በኩል በግብፅ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ተጠሪ በመሆን ለሀገራቸው ሠርተዋል፡፡
በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ሚኒስትር ሆነው ሲሠሩ የነበሩ ሲሆን÷ የካቲት 15 ቀን 2016 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ ነበር፡፡
በዛሬውዕለትም ማለትም ከመስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሰይመዋል ፡፡
በዮሐንስ ደርበው