የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎችና ተቋማት እውቅና ተሰጠ

By Feven Bishaw

October 07, 2024

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በ2016 ዓ.ም በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እና ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል።

በመርሐ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የከተማ አስተዳደሩ ት/ቢሮ ሃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር)፣ የትምህርት አመራሮች፣ ተሸላሚ ተማሪዎችና ወላጆቻቸው ተገኝተዋል፡፡

በመድረኩ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ላፕቶፕና ታብሌቶችን ጨምሮ የተለያዩ ሽልማቶች የተበረከቱ ሲሆን ÷በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገበችው ተማሪ ሲፈኔ ተክሉን ጨምሮ ለሶስት ተማሪዎች የውጭ ሀገር የትምህርት ዕድል ተሰጥቷል፡፡

ከዚህ ባለፈም ተማሪዎቻቸውን ሙሉ ለሙሉ ያሳለፉ የትምህርት ተቋማት ዕውቅና እንደተሰጣቸው የከተማ አስተዳደሩ ት/ቢሮ መረጃ ያመላክታል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ መንግስት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የተማሪዎች ውጤት መሻሻል እያሳየ እንደሚገኝ ገልፀው÷ከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ዘርፉ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር አስገንዝበዋል፡፡

ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በከተማ አስተዳደሩ በ2016 ዓ.ም 21ነጥብ 4 በመቶ ተማሪዎች የማለፊያ ውጤት ማምጣታቸውን እና ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ5 በመቶ እድገት መመዝገቡን ጠቁመዋል፡፡