Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በጋዛ የተጀመረውን ጦርነት አንደኛ ዓመት ምክንያት አድርጎ ሃማስ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል አስወነጨፈ 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃማስ ከእስራኤል ጋር ጦርነት የጀመረበትን አንደኛ አመት አስመልከቶ ወደ እስራኤል ቴል አቪቭን ሮኬቶችን ማስወንጨፉን አስታወቀ፡፡

የሀማስ የጦር ክንፍ የሆነው ኤዘዲን አል ቃሲም ብርጌድ እንዳስታወቀው÷ በፈረንጆቹ 2023 ጥቅምት 7 የተቀሰቀሰውን ጦርነት ምክንያት በማድረግ ቡድኑ ቴል አቪቭ ላይ ጥቃት ፈፅሟል፡፡

በዚህም ቴል አቪቭ ከተማን በሮኬቶች መደብደቡን ገልፆ፤ ጥቃቱ እስራኤል በጋዛ ለምታደርገው ዘመቻ አፀፋ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ከጥቃቱ በኋላ የወጣ ተንቀሳቃሽ ምስል በቴል አቪቭ ከተማ ዳርቻ አካባቢ በሚገኙ ህንፃዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አሳይተዋል።

እስራኤል በበኩሏ ጦርነቱ የተቀሰቀሰበትን ዕለት አንደኛ ዓመት በሃማስ ጥቃት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎችን መዘከሯን ገልጻለች።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የጦርነቱን አንደኛ አመት አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ በዚህ ጦርነት ንፁሃን መከራ ደርሶባቸዋል ብለዋል፡፡

እስራኤል ከሂዝቦላህ ጋር በጀመረችው ጦርነት ምክንያት የቀጠናው ውጥረት ቢባባስም፤ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ሀማስ በእስራኤል ላይ በፈፀመው የሮኬት ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች ሲሞቱ 251 ሰዎች ደግሞ በቡድኑ ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።

በአንፃሩ እስራኤል ከሃማስ ጋር ባደረገችው ጦርነት እስካሁን ከ41 ሺህ በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከ90 ሺህ በላይ የሚሆኑ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የዘገቡት ፕሬስ ቲቪ እና ቢቢሲ ናቸው፡፡

Exit mobile version