የሀገር ውስጥ ዜና

በጋምቤላ ክልል የፖሊዮ ክትባት መሰጠት ተጀመረ

By amele Demisew

October 07, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል የፖሊዮ (የልጅነት ልምሻ) በሽታ የመከላከያ ክትባት መሰጠት መጀመሩን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

ለአራት ቀናት የሚቆየው የክትባት ዘመቻ በሁሉም የክልሉ ወረዳዎችና የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች እየተሰጠ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አቤል አሰፋ እንደገለጹት÷ ክትባቱ ቤት ለቤት ዕድሜያቸዉ ከ5 አመት በታች ለሆኑ 167 ሺህ ህፃናት እንደሚሰጥ ገልፀዋል።

በክልሉ ክትባቱን መስጠት ያስፈለገውም በቅርቡ ሶስት ህፃናት በፖሊዮ ወይም በልጅነት ልምሻ መጠቃታቸው በምርመራ በመረጋገጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለክትባቱ ስኬታማነት የሃይማኖት አባቶች፣የአካባቢ ሽማግሌዎች እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የህጻናቱ ወላጆችና አሳዳጊዎች ትብብር እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።