Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የነዳጅ ግብይት በዲጂታል ሲስተም የክፍያ አማራጮች ብቻ እንዲፈፀም እየሠራሁ ነው- ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2017 በጀት ዓመት በሁሉም የሀገሪቱ ማደያዎች የነዳጅ ግብይት በዲጂታል ሲስተም የክፍያ አማራጮች ብቻ እንዲፈፀም ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሩ የነዳጅ የሪፎርም ስትሪንግ ኮሚቴ በ2017 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ እና በ2016 በጀት ዓመት የነዳጅ ሪፎርም ዕቅድ አፈፃፀም ላይ መክሯል፡፡

በምክክሩም ለስትሪንግ ኮሚቴው የ2017 በጀት ዓመት የነዳጅ ሪፎርም ማስተባበሪያ መሪ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል መባሉን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

በዚህም በበጀት ዓመቱ በሁሉም የሀገሪቱ ማደያዎች የነዳጅ ግብይት በዲጂታል ሲስተም የክፍያ አማራጮች ብቻ እንዲፈፀም በማድረግ በኩል በትኩረት እንደሚሠራ ነው የተገለጸው፡፡

የነዳጅ ሪፎርሙን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ከነዳጅ አቅርቦት፣ ስርጭትና ተደራሽነት አንፃር እየተስተዋሉ ያሉ ክፍተቶችን ለማረም የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግም በዕቅዱ ተመላክቷል፡፡

Exit mobile version