የሀገር ውስጥ ዜና

የአፋር ክልል ተወካዮች ለሀገራዊ ምክክሩ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ አስረከቡ

By amele Demisew

October 07, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል የክልሉን የመጨረሻ አጀንዳ እንዲያደራጁ የተመረጡ 25 ተወካዮች ያደራጁትን አጀንዳ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክበዋል።

ከመስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ቀናት በሰመራ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የአፋር ክልል የምክክር መድረክ ተጠናቅቋል።

የክልሉን መድረክ በበላይነት ሲያስተባብሩ የቆዩት የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች አይሮሪት መሐመድ(ዶ/ር) እና ብሌን ገብረ መድህን(ፕሮፌሰር) የክልሉን አጀንዳዎች ከምክክሩ ባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተረክበዋል።

በምክክሩ ከ49 ወረዳዎች የተለያዩ ማህበረሰቦችን ወክለው የመጡ ከ800 በላይ ወኪሎችን ጨምሮ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከመንግስት አካላት፣ ከተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንዲሁም ከልዩ ልዩ ተቋማትና ማህበራት የተወከሉ ከ700 በላይ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

ኮሚሽነር ብሌን ገብረ መድህን በዚህ ወቅት÷ ከክልሉ የተወሰዱ አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ ምክር ቤት በማቅረብና በመመርመር እንዲለዩ ከተደረጉ በኋላ ለብሄራዊ ምክክር መድረክ ይቀርባሉ ብለዋል።

አይሮሪት መሐመድ ( ዶ/ር ) በበኩላቸው ÷የክልሉ የምክክር መድረክ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ለነበራቸው አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

በምንተስኖት ሙሉጌታ