አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመሰራት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በተገቢ ጥራት በፍጥነት ተጠናቅቀው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስታወቁ፡፡
ከንቲባዋ በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ በመሰራት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ተዘዋውረው መገምገማቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
በዚህም የኮንፍራንስ፣ የቱሪዝምና የስበት ማዕከል ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት የሚያረጋግጡ፣ የኢኮኖሚ መነቃቃትን እና ለነዋሪዎች የሥራ እድልን በሰፊው የሚፈጥሩ የአዲስ ኢንተርናሽናል የኤግዚቢሽንና የኮንፍረንስ ማዕከልን ጎብኝተዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ እየተሰራ ያለውን የለሚ ፓርክ፣ አየር መንገድ-ጎሮን ከአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ጋር የሚያገናኘውን መንገድ ግባታ እና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ ተመልክተዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ በተገቢ ጥራት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው÷ በፍጥነት ተጠናቅቀው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ በቅርበት ክትትል እየተደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡