የሀገር ውስጥ ዜና

በአፋር ክልል የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ከነገ ጀምሮ ይሰጣል

By Meseret Awoke

October 06, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል የፖሊዮ (ልጅነት ልምሻ) መከላከያ ክትባት ከነገ ጀምሮ መሰጠት እንደሚጀምር የክልሉ የህብረተሰብ ጤናና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐመዱ አህመድ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ፥ በክልሉ 6 ዞኖችና 50 ወረዳዎች እንዲሁም ከተማ አስተዳደሮች ለሚገኙ ከ364 ሺህ በላይ ህፃናት ክትባቱ የሚሰጥ ይሆናል።

የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲሰናዱ መቆየቱን ጠቅሰው ፥ አንድም ህፃን ክትባቱን ሳይከተብ መቅረት እንደሌለበት አስገንዝበዋል።

ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ክትባቱን የሚወሰዱ ሲሆኑ ፥ በአፋር ክልል ደረጃ 364 ሺህ 629 ህፃናት የሚከተቡ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለአራት ቀናት የሚሰጠው ይኸው ክትባት ከነገ ጀምሮ የሚሰጥ መሆኑን ያስታወቁት ዳይሬክተሩ ፥ የጤና ባለሙያዎች ለዚሁ ተግባር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የቤት ለቤት ክትባት እንዲሁም በጤና ተቋማትና በትምህርት ቤቶች እንደሚሰጥ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸው ፥ ይህም ከመደበኛው ክትባት ውጭ እንደሆነም አያይዘው ገልፀዋል።

ለዚህ የክትባት ዘመቻው መሣካት የሐይማኖት አባቶችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ ማቅረባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

እንደ ሀገር ነገ የሚጀምረው ክትባቱ በአፋር፣ ኦሮሚያ፣ አማራ እና ጋምቤላ ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚሠጥ መሆኑም ታውቋል።