አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገርን ብሎም ተቋምን ለማገልገል በቅድሚያ የሀገር ፍቅር ስሜት ከዓላማ ፅናት ጋር መላበስ እና እርስ በእርስ መደጋገፍን ባህል ማድረግ እንደሚገባ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ፡፡
ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰልጣኝ የበረራ አስተናጋጆችን በአየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ተቀብለው አነጋግረዋል።
በዚህ ወቅት ዋና አዛዡ ÷ ሀገርን ብሎም ተቋምን ለማገልገል በቅድሚያ የሀገር ፍቅር ስሜት ከዓላማ ፅናት ጋር መላበስ እና እርስ በእርስ መደጋገፍን ባህል ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች ሀገር መሆኗን የገልፁት ዋና አዛዡ ÷ የበረራ አስተናጋጆቹ ውስጣዊ አንድነታቸውን ይበልጥ በማጎልበት ከብሔርተኝነት ከሃይማኖት አክራሪነት እንዲሁም ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ራሳቸውን ሊያርቁ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ መስተንገዶ ሃላፊና አሰልጣኝ መምህርት መሰረት ገላየ በበኩላቸው ÷የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከተሰጠው ሀገራዊ ተልዕኮ ባሻገር ለበርካታ ተቋማት አርዓያ የሚሆኑ የልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡፡
ለዚህም የአየር ሀይሉ አመራሮች ሊመሰገኑ እንደሚገባ ነው ያስገንዘቡት፡፡
በዕለቱም የአየር መንገዱ የበረራ መስተንግዶ ሰልጣኞች የኢትዮጵያን አየር ኃይል ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡