ዓለምአቀፋዊ ዜና

እስራኤል በሌባኖስ በጀመረቸው ዘመቻ ከ440 በላይ የሂዝቦላህ ታጣቂዎችን መግደሏን አስታወቀች

By Mikias Ayele

October 06, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል ባለፉት ሦስት ሣምንታት በደቡባዊ ሊባኖስ ባደረገችው ዘመቻ ከ440 በላይ የሂዝበላህ ተዋጊዎችን መግደሏን የሀገሪቱ ጦር አስታወቀ፡፡

የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ብርጋዲየር ጄኔራል ዳንኤል ሃጋሪ እንደገለፁት ÷ በአየር እና በመሬት ላይ በተደረገው ዘመቻ የፍልስጤም ተሟጋችና የሌባኖስ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ቡድን መሪ የሆኑትን ሀሳን ናስራለህ ጨምሮ በርካታ የቡድኑ አመራሮችን ተገድለዋል፡፡

በዘመቻው ሂዝቦላህን ወደ ሰሜናዊ ሌባኖስ እንዲያፈገፍግ አድርገነዋል ያሉት ቃል አቀባዩ ÷ እስካሁን በተደረገው ዘመቻ ከ30 በላይ የቡድኑ የጦር አዛዦችን ጨምሮ 440 የሂዝቦላህ አባላትን ገድለናል ብለዋል፡፡

ሂዝቦላህ በትላንትናው እለት ብቻ 130 በላይ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል መተኮሱን ገልፀው ፥ የእስራኤል የአየር መከላከያ ጥቃቱን መመከት መቻሉን እና በሌባኖስ የሚያደርገውን ዘመቻ አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

ሂዝቦላህ በበኩሉ ÷እስራኤል በድንበር አካባቢ የምትገኘውን ኦዳይሴህ ከተማን ለመቆጣጠር ያደረገችውን ሙከራ ማክሸፉን ገልፆ ፤ እስራኤል የምታደርገውን መጠነ ሰፊ ዘመቻ እየመከተ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ከሂዝቦላህ በተጨማሪ የእስራኤል መከላከያ ኃይል ለኢራን የባላስቲክ ሚሳኤል ጥቃት የአፀፋ ምላሽ ለመስጠት ወታደራዊ እቅድ ማውጣቱ ተገልጿል፡፡

የእስራኤል ወታደራዊ ሀይል እንዳስታወቀው ÷ ኢራን ከ200 በላይ ሚሳኤሎችን ወደ ቴል አቪቭ በመተኮስ በእስራኤል የአየር ማረፊያዎች ላይ ጉዳት አድርሳለች፡፡

ለኢራን ጥቃትም የእስራኤል ጦር ከበድ ያለ ሲል የገለጸውን የአፀፋ ጥቃት በሣምንቱ መጀምሪያ አካባቢ ለመፈጸም እቅድ ማውጣቱን አስታውቋል፡፡

የኢራኑ መንፋሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ በበኩላቸው ÷ እስራኤል በጋዛ እና በሌባኖስ ለምታድርገው ዘመቻ ተጨማሪ አጸፋ እንደሚጠብቃት ገልፀው ፤ እስራኤል በቅርቡ ትጠፋለች ማለታቸውን የዘገበው አር ቲ ነው፡፡