Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሆረ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ተከብሮ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሆረ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል በቢሾፍቱ ከተማ ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት ተከብሮ መጠናቀቁን አባ ገዳ ጎበና ኦላ አስታውቀዋል።

አባ ገዳ ጎበና ኦላ በሰጡት መግለጫ፥ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የእርቅና ወንድማማችነት በዓል የሆነው ሆረ አርሰዲ ኢሬቻ በድምቀት ተከብሮ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ አባገዳዎችና ሀደ ሲንቄዎች፣ቄሮዎች እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

ሆረ አርሰዲና ሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ ያለምንም የጸጥታ ችግር በድምቀት እንዲከበር ያደረጉ የጸጥታ አካላትንም አመስግነዋል።

 

የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ጀሚላ ሲምብሩ፥ የኢሬቻ በዓል ከባህላዊ መገለጫነቱ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው  ከጊዜ ወደ ጊዜ እጨመረ መምጣቱን አስገንዝበዋል።

የገዳ ሥርዓት መገለጫ የሆነውን የኢሬቻ በዓል የቱሪስት መዳረሸነቱን ለማሳደግና በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በትኩረት እንደሚሰራ አንስተዋል።

የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ፥ በከተማዋ የሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በቂ አቅርቦት እና አገልግሎት ለእንግዶቹ በመስጠት ለበዓሉ በድምቀት መከበር አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ በዓሉ በስኬትና በድምቀት ተከበሮ እንዲጠናቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት  ምስጋና ቀርቧል።

 

በመላኩ ገድፍ እና ዳግማዊ ዴክሲሳ

 

Exit mobile version