የሀገር ውስጥ ዜና

“የሆረ ፊንፊኔ እና የሆረ አርሰዴ የኢሬቻ በዓላት በስኬት መጠናቀቃቸዉ የኦሮሞን ህዝብ ታላቅነት የሚያረጋግጥ ነው”- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

By Feven Bishaw

October 06, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2017(ኤፍ ቢ ሲ)”የሆረ ፊንፊኔ እና የሆረ አርሰዴ የኢሬቻ በዓላት በስኬት መጠናቀቃቸዉ የኦሮሞን ህዝብ ታላቅነት ያረጋገጡ ናቸው”ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ፡፡

ርእሰ መስተዳደሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ÷የሆረ ፊንፊኔ እና የሆረ አርሰዴ የኢሬቻ በዓላት ያለአንዳች እንከን እሴቱን በጠበቀ አኳኋን በስኬት መጠናቀቃቸዉን ገልፀዋል፡፡

በዚህም የኦሮሞ ህዝብ ሰላም ወዳድ፣ ለአንድነትና ለወንድማማችነት ክብር ያለዉ፣ በተግባርም ባህላዊ እሴቶቹን የተላበሰ መሆኑን ዳግም በማረጋገጡ በራሴና በኦሮሚያ ክልል መንግስት ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡

ከአባቶቻችን የተቀበልነውን ቃል-ኪዳን ጠብቀን እነሱ የከፈሉልንን መስዋእትነት በድል ከፍ አድርገን እነሆ ድካማቸዉ ፍሬ አፍርቶ ዛሬ ህዝባችን በተሟላ ነጻነት ዉብ ባህሉን ለአለም ከማሳየት አልፎ የሀገራችንን መልካም ገጽታ በመገንባት ላይ ይገኛል ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ይህ ትልቅ ድል ነዉ ብለዋል፡፡

ትላንት እና ዛሬ በሆረፊንፊኔ እና በሆረ ሃርሰዴ የኢሬቻ በዓላት ላይ የተቀዳጀነው ስኬት ጠንካራ አንድነት ያለን እና አቃፊ መሆናችንን ያረጋገጠ፤ ዉድቀታችንን ለሚጠባበቁት ዉርደትን ያከናነበ፤ ደስታችንን ለተካፈሉት ደግሞ ክብርን ያጎናጸፈ ሆኗል ሲሉም ገልፀዋል፡፡

በዚህም አንድነት ካለ ያቀድነዉን ሁሉ መፈጸም እንደምንችል ያረጋገጥንበት ሆኖ በአሉን ለማክበር ከመጡት ጋር አክብረን፣ ለጉብኚት የመጡትን ደግሞ ለዘመናት የዳበረዉን ቱባ ባህላችንን በማስጎብኘት በስኬት አጠናቅቀናል፡ ብለዋል፡፡

ለዚህም የኦሮሞን ህዝብ፣ አባ ገዳዎች፣ ሃዳ ሲንቄዎች፣ ፎሌዎች፣ ቄሮና ቀሬዎች፣ የክልሉ አመራሮችና በየደረጃዉ ያሉ መዋቅሮች፣ የክልሉና የፌደራል የጸጥታ ተቋማት፣ በአጠቃላይ የክልሉ ህዝብን በሙሉ ከዋዜማዉ አንስቶ እስከ ማጠናቀቂያዉ ድረስ በዓሉ በሰላምና በተረጋጋ መንፈስ እንዲከበር እንዲሁም የበአሉ ተሳታፊዎች ያለአንዳች ችግር በሰላም ወጥተዉ እንዲገቡ ማድረግ በመቻላቸውም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ኢሬቻ የእርቅ፣ የሰላም፣ የአንድነትና የወንድማማችነት አርማ መሆኑን ለሙያቸው በመታመን በተለያዩ ቋንቋዎች ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ጆሮ ላደረሱ ለሀገር ውስጥና ለዉጪ ሚዲያዎችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ከኢሬቻ የወረስናቸዉን የአንድነትና የወንድማማችነት፤ የይቅርታና የፍቅር እንዲሁም የሰላም እሴቶችን በመጠቀም በ2017 ኢሬቻን ለባህላችን ህዳሴ በማዋል የጀመርነዉን ልማት በሁሉም ዘርፎች የምናሳካበት፤ የኦሮሞ አንድነት የሚጸናበትና የሀገራችን ህብረ-ብሄራዊነት ይበልጥ የምናጠናክርበት እንዲሆንልንም እመኛለሁ ብለዋል፡፡