የሀገር ውስጥ ዜና

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለጤናው ዘርፍ መልካም ዕድል ይዞ መጥቷል – ዶ/ር መቅደስ ዳባ

By Melaku Gedif

October 05, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በቅርቡ ወደ ሙሉ ትግበራ የገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የጤና ዘርፉን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

6ኛው ሀገር አቀፍ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ዓመታዊ ጉባኤ ‘ዲጂታላይዜሽን፤ ለማይበገር የአቅርቦት ሰንሰለት’ በሚል መሪ ሀሳብ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም አጋሮች በተገኙበት በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

በጉባኤው ላይ ዶ/ር መቅደስ ዳባ እንደተናገሩት፤ በመድኃኒት፣ በህክምና መሳሪያዎችና ግብዓት አቅርቦት ለአህጉሩ ተሞክሮ ሊሆኑ የሚችሉ ስራዎች ተሰርተዋል።

በተለይም የአቅርቦት ስርዓቱን ለማሳደግና ሂደቱን ቀልጣፋ ለማድረግ አበረታች ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

ከሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ትምህርት በመውሰድ ቀልጣፋ የአቅርቦት ስርዓት መፍጠር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

መድኃኒትና የህክምና ግብዓት ተጠቃሚው ጋር የሚደርስበትን ጊዜ ለማስተካከልም የአቅርቦት ሰንሰለት ስርዓቱን ለማዘመን ከአጋሮች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ስኬት መመዝገብ መጀመሩን ጠቁመዋል።

አቅርቦቱን ይበልጥ ቀልጣፋና ፍትሀዊ ለማድረግ በየደረጃው ያለው አመራርና ባለሙያ ቁርጠኛና ታማኝ ሆኖ መስራት እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል።

የመድኃኒት፣ የህክምና መሳሪያዎችንና ግብዓቶችን አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ እንደሀገር ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰው፤ በተለይም የሀገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ ሀገር በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለጤናው ዘርፍ መልካም እድሎችን ይዞ መምጣቱንም ተናግረዋል።

በተለይም በግዥ ስርዓቱ የሚገጥምን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከመቅረፉም ባሻገር በማሻሻያ ድጎማ ከተደረገባቸው መካከል የመድሃኒት አቅርቦቱ አንዱ መሆኑን መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።