አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአደባባይ ክብረ በዓላት ለህዝቦች ወንድማማችት መጠናከር፣ ለከተማዋ ገፅታ ግንባታ፣ ለቱሪዝም እድገት ያላቸውን አስተዋፅኑ በመገንዘብ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ማስተናገዳችንን እንቀጥላለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ ሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል እሴቱን ጠብቆ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ተጠናቋል ብለዋል፡፡
በዓሉን ለማክበር የታደሙ አባገዳዎች፣ ሀደሲቄዎች፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች፣ የከተማዋ ነዋሪዎች በድጋሚ የሰላም እና ፍቅር መገለጫ የአብሮነት የእሴት ገመድ ሆረ ፊንፊኔ በዓል አከባበር እና ስኬት እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ለክብረ በዓሉ መሳካት ነዋሪዎች፣ ለፀጥታ አካላት፣ የሚዲያ፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ወጣቶች፣ የሆቴል ባለ ሀብቶችና ሰራተኞች፣ የኦሮሚያ ክልል እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ በጠቃላይ በዓሉ እንዲከበር አስተዋፅኦ ላበረከቱ ሁሉ አመስግነዋል፡፡
ነዋሪዎች እንግዶችን እንኳን አደረሳችሁ እያሉ በማስተናገድ አክብሮታቸውን፣ ደስታቸውን ፣ አብሮነታቸውን እና የወንድማማችነታቸዉን በፍቅር አሳይተዋል ብለዋል፡፡
የአደባባይ ክብረ በዓላት እና ኩነቶች ለህዝቦች ወንድማማችት መጠናከር፣ ለከተማችን ገፅታ ግንባታ፣ የኢኮኖሚ መነቃቃት እና የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እድገት ያለውን አስተዋፅኑ በመገንዘብ በኢትዮጵያዊ በጨዋነት ማስተናገዳችንን እንቀጥላለንም ሲሉም ገልጸዋል፡፡