Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ፖሊስ የ ‘ሆረ ፊንፊኔ’ ኢሬቻ በዓል በድምቀት ተከብሮ መጠናቀቁን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2017 ዓ.ም የ ‘ሆረ ፊንፊኔ’ ኢሬቻ በዓል በድምቀት ተከብሮ መጠናቀቁን የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ፖሊስ ባወጣው መግለጫ÷ አባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ፣ ከጎረቤት ሀገራት የመጡ እንግዶች እና የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች የታደሙበት ‘ሆረ ፊንፊኔ’ በድምቀት ተከብሮ ተጠናቅቋል ብሏል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታና ደኅንነት አካላት ጋር በመቀናጀት አስቀድሞ የስጋት ቦታዎችን ለይቶ በማጥራት በቴክኖሎጂ የታገዘ በርካታ የፀጥታ ኃይል አሰማርቶ÷ ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ፣ ከበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴዎችና ከሰላም ሠራዊት ወጣቶች ጋር ተባብሮ በመሥራት በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ አስችሏል ነው ያለው፡፡

ለዚህም ለአባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ለበዓሉ ታዳሚዎች፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፣ ለበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴዎች እና ለሰላም ሠራዊት ወጣቶች እንዲሁም ኃላፊታቸውን በትጋት ለተወጡ የፀጥታና ደኅንነት አካላት ፖሊስ ምስጋና አቅርቧል፡፡

ነገ በቢሾፍቱ ከተማ የሚከበረው የ‘ሆረ ሀርሰዲ’ ኢሬቻ በዓልም ያለምንም የፀጥታ ችግር በድምቀት እንዲጠናቀቅ ሕብረተሰቡ ለፀጥታና ደኅንነት አካላት የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል፡፡

Exit mobile version