አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 2 ሺህ 593 ተማሪዎች አስመረቀ፡፡
ተመራቂዎቹ በመደበኛ፣ በተከታታይና በክረምት መርሐ-ግብሮች ትምህርታቸውን የተከታተሉ እና በ2016 ዓ.ም መመረቅ የነበረባቸው ናቸው ተብሏል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ዩኒቨርሲቲው በትምህርት፣ በጥናትና ምርምር እና በማኅበረሰብ አገልግሎት የሚሰጠውን አገልግሎት በብዛትና በጥራት እያሳደገ ነው ብለዋል፡፡
በየጊዜው የሚገጥሙትን ፈተናዎች ወደ ዕድልና ጥንካሬ እየቀየረ የመጣ አንጋፋ ተቋም መሆኑን ገልጸው÷ የካምፓሶቹን እና ኮሌጆቹን ቁጥር እያሳደገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የዕለቱን የክብር እንግዳ ወዳጀነህ መሐረነ (ዶ/ር) ጨምሮ ተመራቂ ተማሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡
በየሻምበል ምኅረት