እንኳን ለ2017 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን!
የሰላም፣ የአንድነትና የብራ ንጋት መልካም ምኞት ምልክት የሆነው ኢሬቻ፤ የኦሮሞ ህዝብ በጋራ ወጥቶ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት ትልቅ በዓል ነው።
ዝናብ ሰጥቶ ያበቀለውን ፈጣሪ፣ የክረምቱን ጎርፍና በረዶ በሰላም አሳልፎት ብሩህ በሆነና በተስፋ ወደ ተሞላው ብራ ያሻገረውን ፈጣሪ፤ ለማመስገን ወደ መልካ (ወንዝ) ወጥቶ የኢሬቻን ስርዓት ይፈጽማል።
ብራ ለፍጥረት ሁሉ ልዩ ነው። ለሁሉም የሚተርፍ ነገር አለው። ብራ ምድሩ በልምላሜ ተሞልቶ፣ በአበቦች ውበት አጊጦ፣ ጋራው ሸንተረሩ ዓይንን የሚማርክበት ወቅት ነው። የአበቦች መዓዛ አካባቢን የሚያውድበት ጊዜ ነው።
እንስሳት እንደልብ ግጦሽ የሚያገኙበት ነው፤ ክረምቱን በቀፎ ውስጥ በረሃብ ያሳለፉት ንቦች ወጥተው አበቦችን እያማረጡ በመቅሰም ማር ለመስራት የሚታትሩበትም ነው።
ብራ ክረምቱን ተሸሽገው የቆዩ አዕዋፍ ዜማ እያሰሙ የሚጠራሩበትና የሚፈላለጉበት ወቅት ነው። ስለ ዜማ ከተነሳ አዕዋፋት ብቻ ሳይሆኑ ወጣቶችም እያዜሙ የሚፈላለጉበትና የሚገናኙበት ወቅት ነው።
ኦሮሞም በዚህ ውብና በተስፋ በተሞላ ወቅት የክረምቱን አስቸጋሪ ጊዜ አሳልፎት በሁሉም ነገር ወደተትረፈረፈ ብራ ላሻገረው ፈጣሪው በጋራ እውቅና ይሰጣል፤ በህብረትም ምስጋና ያቀርብለታል።
በኢሬቻ እርጥብ ሣር ይዞ ወደ መልካ (ወንዝ) በመውጣት አንዱ ለሌላኛው ያለውን ክብር የሚያሳይበት፣ የተጣላ ይቅር የሚባባልበት፣ ለፈጣሪው ያለውን ምስጋና የሚገልፅበት ነው።
በድጋሚ እንኳን ለ2017 የኢሬቻ በዓል በሰላም አደረሳችሁ እላለሁ!