የሀገር ውስጥ ዜና

ለሀገር ግንባታ የሚውሉ ሕዝባዊ በዓላት እውቅና እንዲያገኙ እንሠራለን – አቶ አደም ፋራህ

By ዮሐንስ ደርበው

October 04, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘመን ተሻጋሪ የትውልድ ዐሻራ ከማኖር በተጨማሪ ለሀገር ግንባታ የሚውሉ ሕዝባዊ በዓላት ተገቢውን እውቅና እና ክብር እንዲያገኙ እንሠራለን ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ማስተባባሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

አቶ አደም ለ2017 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም÷ ባህላዊና ትውፊታዊ ቅርሶቻችን የሀገር ግንባታ መሳሪያ ሆነው እንዲያገለግሉ አበክረን እንሰራለን ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ባህላዊና ትውፊታዊ ቅርሶቻችን የሀገር ግንባታ መሳሪያ ሆነው እንዲያገለግሉ አበክረን እንሰራለን!!

ሕዝባዊ በዓላት በሕዝቡ ባለቤትነት ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፉ፣ ማኅበራዊ ትስስር እንዲፈጥሩ፣ የሀገር ግንባታ መሳሪያ ሆነው እንዲያገለግሉና ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን እንዲያጠናክሩ ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል።

በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ያሉ የሕዝብ ሀብት የሆኑ የጋራ እሴቶችና ባህሎች የሚንፀባረቅባቸውን በዓላት ተገቢውን ክብርና ትኩረት እንዲያገኙ በማድረግ በሰራነው ስራም የሀገራችንን ኅብረ ቀለማዊ ሀምራዊነት ከሀገር ውስጥ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊያሳዩ የሚችሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በዚህም መንግሥት ሚናውን መርኅንና ሕዝብ የሰጠውን ኃላፊነት መሰረት በማድረግ ባደረገው ድጋፍ በርካታ ሕዝባዊ ባህላዊና ትውፊታዊ ቅርሶቻችን በዩኔስኮ የተመዘገቡ ሲሆን÷ ሕዝብ ይበልጥ ባለቤት ሆኖ እንዲጠብቃቸው፣ እንዲንከባከባቸውና ብሔራዊ ኩራትን እንዲጎናፀፍባቸው ተጨማሪ ዕድሎችን ፈጥሮልናል።

ይህንንም ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በቀጣይም በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ዘመን ተሻጋሪ የትውልድ ዐሻራ ከማኖር በተጨማሪ ከሕዝብ የተቀዱና ለሀገር ግንባታ የሚውሉ እንደ ኢሬቻ ያሉ ሕዝባዊ በዓላት ተገቢውን እውቅና እና ክብር እንዲያገኙ ልዩ ትኩረት ሰጥተን እንደምንንቀሳቀስ ለመግለፅ እወዳለሁ።

መልካም የኢሬቻ በዓል!!!