አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከፓኪስታን እስላማዊ ሪፐብሊክ የብሔራዊ ሸንጎ አፈ-ጉባዔ ሰርዳር አያዝ ሳዲቅ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም፤ የፓርላማ ቻናሎችን በመጠቀም በፓኪስታን የተመሠረተውን የኢትዮ-ፓኪስታን የፓርላማ ወዳጅነት ቡድን አቻ አካል በኢትዮጵያ ስለ ማቋቋም መክረዋል።
በተጨማሪም ሀገራቱ በመካከላቸው ያለውን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብር ለማሳደግ በሚያስችሉ መስኮች ላይ መክረዋል።
አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለቀጠናው እድገት የወሰደቻቸውን ተነሳሽነቶች እና ሰላምና ደህንነትን በማስፈን ረገድ ስለምትጫወተው ወሳኝ ሚና ገለጻ አድርገዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ያመጣው ውጤትን በተመለከተም ፖሊሲው የኢትዮጵያን ምርታማነት የሚጨምር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን የሚያሣድግ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ እና የፓኪስታን ግንኙነት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በኢስላም አባድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መከፈት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ካራቺ በረራ መጀመር እና የንግድ ልዑካን ቡድኖች ልውውጥ ለእድገቱ ማሣያ በአብነት አንስተዋል።
በፈረንጆቹ 2025 መጀመሪያ ላይ በአዲስ አበባ የፓኪስታን የንግድ ትርኢት እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።
አፈ-ጉባዔ ሰርዳር አያዝ ሳዲቅ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አህጉር የምታገናኝ በር መሆኗን ገልጸው፤ በፓኪስታን “ሉክ አፍሪካ” እና “ኢንጌጅ አፍሪካ” ፖሊሲ ውስጥ ማዕከላዊ ሚና ለመጫወት አቅም ያላት ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።
የፓኪስታን መንግስት በአፍሪካ ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኑን መግለጻቸውን በፓኪስታን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመልክቷል።