Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢሬቻ ለሰላም እሴት ግንባታ የጎላ ፋይዳ አለው – ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢሬቻ ለሰላም እሴት ግንባታ የጎላ ፋይዳ አለው ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ተናገሩ፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ የኢሬቻ በዓልን አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ብዝሀ ማንነትና ባህሎች ተከባብሮና ተቻችሎ የሚኖሩባት ማዕከል ናት ብለዋል።

ከነዚህ ውብ ባህልና ዕሴቶች አንዱ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የኢሬቻ በዓል መሆኑን ገልጸው፤ ኢሬቻ የክረምት ወራት አልፈው መጸው ሲገባ ፈጣሪ የሚመሰገንበት በታላቅ ሥነ ሥርዓት የሚከበር በዓል በመሆኑ ተናግረዋል።

በአከባበሩ የኢሬቻ ባህላዊና ታሪካዊ ዕሴቶችን በማጉላት ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ማዋል እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢሬቻ በዓል የቱሪዝም ዘርፉን በማጠናከር ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ መድረኮች ማስተዋወቅ፣ መጠበቅና መንከባከብ እንዲሚገባ አስገንዝበዋል።

ኢሬቻ አንድነትና ህብረብሔራዊ ወንድማማችነት/እኅትማማችነት በማጠናከር ለሠላም ዕሴት ግንባታ የጎላ ፋይዳ እንዳለው አንስተው÷ በዓሉ በህዝቦች መካከል ያለውን ግኑኝነት የሚያጠናክር መሆኑን አስረድተዋል።

Exit mobile version