አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መሥተዳደር አሻድሊ ሃሰን በክልሉ ለሚገኙ የአቅመ ደካማ ቤተሰብ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ፡፡
ድጋፉ ደብተር እና እስክርቢቶ ሲሆን አጠቃላይ ዋጋው ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
አቶ አሻድሊ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት “አንድም ሕጻን በቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጪ አይውልም” በሚል መርኅ የክልሉ መንግሥት ባለሃብቶችን በማስተባበር ያሰባሰበው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ድጋፉን የተረከቡ የዞኖች፣ የከተማ እና የልዩ ወረዳ አሥተዳዳሪዎች በበኩላቸው ሁሉም ተማሪዎች ትምህርት እንዲከታተሉ እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸው÷ ድጋፉ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል እናደርጋለን ብለዋል፡፡