አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ የካቲት ወር 2020 የአፍሪካ ሀገራት ምድር ጦር ጉባኤን ታስተናግዳለች።
ጉባኤውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በአፍሪካ የአሜሪካ ጦር ጋር በመተባር ያዘጋጀዋል።
በአፍሪካ የአሜሪካ ጦር ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ላፍቴ ፍሎራ በጉባኤው ዝግጅት ዙሪያ ለመምከር ጉብኝት አድርገዋል።
በጉብኝታቸውም ወቅት ለጉባኤው እየተደረገ ባለው ዝግጅት ዙሪያ ከኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ሀላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
የአሜሪካ ጦር በአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት ጥረቶችን ማገዝ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
ለአራት ቀናት የሚካሄደው ጉበኤ ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ወታደራዊ አዛዦችን የሚያሰባስብ ነው።
በዚህ ቆይታቸው በሀገራቱ መካከል ወታደራዊ ትብብርን በማጠናከር የአህጉሪቱን ደህንነት መጠበቅ ላይ እንደሚወያዩ በአፍሪካ ከአሜሪካ ጦር እዝ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።