አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል ዛሬ ጠዋት በሊባኖስ ላይ አዲስ መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት መፈፀሟ ተገለፀ፡፡
ጥቃቱን ተከትሎ የዳሂየህ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ በበርካታ አካባቢዎች ከፍተኛ ፍንዳታ መከሰቱ ተነግሯል።
የሂዝቦላህ ጠንካራ ምሽግ እንደሆነ የሚነገርለት የዳሂየህ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ከአየር ጥቃቱ በኋላ ዛሬ ጠዋት በእሳት ተያይዞ ነበር ተብሏል፡፡
ጥቃቱ በቅርቡ በእስራኤል የአየር ጥቃት የተገደሉትን የሂዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ ይተካሉ የተባሉትን የአጎታቸውን ልጅ ሀሽም ሳፊዲንን ኢላማ ያደረገ እንደነበር ተመላክቷል፡፡
የሊባኖስ የህዝብ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው÷ ባለፉት 24 ሰአት ውስጥ በተፈፀመው የምድር እና የአየር ጥቃት 37 ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች 151 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
እንደሊባኖስ ባለስልጣናት መረጃ ደግሞ እስራኤል ላለፉት ሁለት ሳምንታት ባካሄደችው ዘመቻ ከ1 ሺህ 300 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከ1 ሚሊዮን በላይ ደግሞ አካባቢያቸውን ለቀው ወጥተዋል፡፡
እስራኤል ባለፉት ሶስት ቀናት በደቡባዊ ሊባኖስ እያካሄደች ባለችው ዘመቻ ከተለያዩ ወታደራዊ ክፍሎች ዘጠኝ ወታደሮች እንደሞቱባት የሀገሪቱ ጦር አስታቀውቋል፡፡