አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ከ9 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ ሕገ-ወጥ መድሃኒትና ጦር መሳሪያ መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኢንስፔክተር ደበበ ኦንቶ እንዳሉት÷ ሕገ ወጥ ዕቃዎቹን የጫነው ተሽከርካሪ መነሻውን ኮንሶ ዞን አድርጎ ወደ ጋሞ ዞን ገረሴ ከተማ ሲጓዝ ነው በሕብረተሰቡ ጥቆማ የተያዘው፡፡
በሕገ-ወጥ መንገድ የተያዘው 28 ሺህ 260 ስትሪፕ የወባ መድሃኒት 9 ሚሊየን 891 ሺህ ብር ግምታዊ ዋጋ እንዳለው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በጋሞ ዞን ብርብረ ከተማ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ከብሔራዊ መረጃ ደህንነት በደረሰ ጥቆማ ከግለሰብ ቤት መያዙን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡