የሀገር ውስጥ ዜና

አፈ-ጉባኤ ታገሠ ጫፎ ከጀርመን ፓርላማ ልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ

By Shambel Mihret

October 03, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሠ ጫፎ የጀርመን ፓርላማ ልዑካንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ውይይት አደረጉ።

አፈ-ጉባዔ ታገሰ በጀርመን የፓርላማ አባልና የኮንራድ አዴናወር ስቲፍትንግ ምክትል ሊቀ-መንበር ሔርማን ግሮሔ እና ልዑካን ቡድናቸው ጋር ኢትዮጵያ ከጀርመን ጋር በሚኖራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ መክረዋል።

ውይይቱም በኢትዮጵያና ጀርመን መካከል ስላለው የቆየ የሁለትዮሽ ግንኙነትና በቀጣይም በሁለቱ ሀገራት ሊኖር የሚችል የግንኙነት ዕድሎች ላይ ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ ከጀርመን ጋር በሥራ ዕድል ፈጠራና በአነስተኛና በጥቃቅን ኢንዱስትሪዎች ልምድ መካፈል እንደምትሻ እንዲሁ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዋን ለውጭ አልሚዎች ክፍት በማድረጓ በግብርና፣ ማዕድን፣ በቱሪዝምና ሌሎች ዘርፎች የቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ዕድል መኖሩን አፈ-ጉባኤው ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያና ጀርመን በኢኮኖሚና በንግድ በጋራ መስራት እንደሚችሉ መገለጹንም ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የጀርመን ምክር ቤት ልዑክ የኢትዮጵያ ፓርላማን ጨምሮ ከሌሎች ተቋማት ጋር ውይይት ለማድረግ እንደሚፈልጉም ገልፀዋል።

በዚሁ ወቅት አፈጉባዔ ታገሰ እንዳሉት ÷ በዜጎች የሚነሱ ጉዳዮች በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኩል ምላሽ እንዲያገኙ መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው።

በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የተቋቋመው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሊያካሄድ ያለመው ምክክር የተረጋጋችና ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ መደላድል ለመፍጠር አጋዥ እንደሚሆን ትልቅ እምነት አለንም ብለዋል።

የልዑካን ቡድኑ መሪ ሔርማን ÷ ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር በፖለቲካ፣ በትምህርት፣ ሠላም፣ ነፃነት እና ፍትህ በጋራ ለመስራት ያላትን ቁርጠኝነት ገልፀዋል::