አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የብር ሸለቆ መሰረታዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በዛሬው እለት ለ40ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን መሰረታዊ ወታደሮች አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ርዓቱ ላይ የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡
ተመራቂ የሠራዊት አባላቱ በሥልጠና ቆይታቸው በሙያው በቂ ወታደራዊ ዕውቀት እና በተግባር የታገዘ ወታደራዊ ልምድ ማግኘታቸውንና ለተልዕኮም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የብርሸለቆ መሰረታዊ የውትድርና ማስልጠኛ ት/ቤት ዋና አዛዥ ኮለኔል መኮነን መንግስቴ በዚሁ ወቅት ÷ 40ዙር ሰልጠኞች የአካል ብቃት፣ የተኩስ እና ልዩ ልዩ ወታደራዊ ስልጠናዎች ያጠናቀቁ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ሠልጣኞቹ በወታደራዊ ዲስፕሊን የታነጹ እና እስከ ሕይዎት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ናቸው ብለዋል።
ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን በበኩላቸው እንዳሉት÷ ተመራቂዎች ሀገርንና ህዝብን አስቀድመው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሳይበግራቸው ስልጠናቸውን በተገቢው መንገድ ማጠናቀቃቸው ትልቅ ድል ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በየዘመኑ ያጋጠሟትን ችግሮች በጀግኖች ልጆቿ እየተወጣች መምጣቷን ያነሱት ጄነራሉ ÷ አሁንም በጀግኖቿ ሉአላዊነቷን አስጠብቃ ትቀጥላለችም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ያለንበት ቀጣና ግጭት የማያጣው እና የተለያዩ ትንኮሳዎች ያሉበት በመሆኑ የሰለጠነ የተደራጀ ሠራዊት መገንባት ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስከበር የግድ ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም ከዚህ አንፃር የሰለጠነ የሰው ኃይል ግንባታ ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንዳለም ተገልጿል።
ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚፈታተን የትኛውም ኃይል ጥቃት ለመከላከል በሚያደርገው ዝግጅት ተጨማሪ አቅም ስለሆናችሁ የ40ኛውን የብር ሸለቆ መሰረታዊ ውትድርና ሰልጣኝ ምሩቃንን ልዩ ያደርጋቸዋል ብለዋል።
በበረከት ተካልኝ