አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ባሳለፍነው ማክሰኞ ከየመን ወደ ጅቡቲ ሲጓዙ የነበሩና በአደጋው በርካቶች የሞቱ ዜጎች በሙሉ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው መረጋጋገጡ ተሰምቷል፡፡
መስከረም 21/2017 ዓ.ም ማምሻውን ከየመን ወደ ጅቡቲ 320 መደበኛ ያልሆኑ ፍልሰተኞች ይዘው የተነሱት ሁለት የስደተኞች ጀልባዎች በጅቡቲ ባህር ዳርቻ አከባቢ ሲደርሱ በደረሰው አደጋ የዜጎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።
አደጋውን ተከትሎ 48 ፍልሰተኞች ህይወታቸው ሲያልፍ፣ 197 ፍልሰተኞች ከአደጋው ተርፈው ኦቦክ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የስደተኞች ካምፕ ደርሰዋል ነው የተባለው።
የተቀሩት 75 ፍልሰተኞችን አካል የማፈላለጉ ስራ በነፍስ አድን ሠራተኞች መቀጠሉ ተጠቁሟል።
እስከአሁን በስፍራው በተደረገው የዜጎች ማጣራት ሂደት ሁሉም ፍልሰተኞች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ከሚመለከተው አካላት በተገኘው መረጃ ማወቅ መቻሉን የዘገበው በጅቡቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ነው።
ኤምባሲው በዚህ ከባድ አደጋ ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ ዜጎቻችን የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል፡፡
ኤምባሲው አክሎም ፥ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ምክንያት በየጊዜው እያደረሰ ያለውን ሞት ለመቀነስ ሁሉም ተቋማት በርብርብ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
ኤምባሲው ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እያሳሰበ ፤ በቀጣይ መንግስት እነዚህ ግለሰቦች ላይ ጠንካራ እርምጃ የሚወስድ መሆኑንም ከገጹ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።