ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አ.ማ እና ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት አ.ማ በማዋሀድ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን አ.ማ በሚል መጠሪያ ለመጠራት ወስነዋል፡፡
ለተመሳሳይ ዓላማ በተመሳሳይ ባለአክሲዮኖች የተቋቋሙት እነዚህ ማህበራት ውህደቱን የሚፈጽሙበት ዋነኛ ምክንያት የፋይናንስ፣ የሰው ሀይል፣ የቴክኖሎጂ እና የመሰረተ ልማት አቅምን በማቀናጀት የሀብት ብክነትን ለማስቀረት እና ትርፍማነትንና ውጤታማነትን ለማሳደግ በማሰብ ነው፡፡
ማህበራቱ ውህደቱን የሚፈጽሙት በአዋጅ ቁጥር 1243/2013 በወጣው አዲሱ የንግድ ህግ አዋጅ መሰረት ሲሆን ሰፊ ጊዜ በመውሰድ የውህደት እቅድ አዘጋጅተው በማህበራቱ የተናጠልና ጠቅላላ ጉባኤዎች በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል፡፡
የውህደቱ ሂደት በህግ መሰረት የሚመራ፣ የባለሀብቶቹን እና የ3ኛ ወገኖችን ጥቅም ባከበረ መልኩ መፈጸሙን የሚከታተሉ ገለልተኛ ገምጋሚ ባለሙያዎችን መድበው ሲከታተሉ ቆይተዋል፣ የውህደት ሂደት ሪፖርትም ቀርቦ ፀድቋል፡፡
የማህበራቱ የውህደት እቅድ፣ የማህበራቱ ጠቅላላ ጉባኤ የውህደት እቅዱን በሙሉ ድምጽ ያጸደቀበት ቃለ ጉባኤ እና የገለልተኛ ገምጋሚ ባለሙያዎች ሪፖርት አዲስ አበባ፣ ልደታ ክ/ከ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አጠገብ ከሚገኘው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አ.ማ ህንጻ ውስጥ ይገኛል፡፡
በመሆኑም ውህደቱን በተመለከተ ጥያቄ አለኝ የሚል ባለመብት ጥያቄያቸውን ከላይ በተገለጸው አድራሻ ይህ ማስታወቂያ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ባሉት 30 ተከታታይ ቀናት ለማቅረብ ይችላሉ፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በስልክ ቁጥሮች፡- 011-551-67-77 ወይም 011-550-44-51 ደውሎ ማነጋገር ይችላሉ፡፡
የውህደቱ አመቻች ኮሚቴ