አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል በሊባኖስ በተመረጡ የሂዝቦላህ ይዞታዎች ላይ የምትፈጽመው የአየር ላይ ጥቃት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቃለች፡፡
በዛሬው ዕለትም በሊባኖስ መዲና ማዕከላዊና ደቡባዊ ቤሩት በተመረጡ ቦታዎች ላይ የተሳካ የአየር ጥቃት መፈጸሙን የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት አስታውቋል፡፡
ጥቃቱን ተከትሎም እስካሁን የ9 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን÷ 14 ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱን የሊባኖስ ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በደቡባዊ ሊባኖስ የእስራኤል ጦር ከሂዝቦላህ ታጣቂዎች ጋር የፊት ለፊት ውጊያ እያደረገ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
በውጊያው 8 የሚደርሱ ወታደሮቹ መገደላቸውን የገለጸው የእስራኤል ጦር÷ በቀጣናው በሂዝቦላህ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል፡፡
ስለሆነም በደቡባዊ ሊባኖስ ተጨማሪ 25 አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች አካባቢውን በፍጥነት ለቀው እንዲወጡ ጦሩ አሳስቧል፡፡
የሂዝቦላህ ታጣቂዎች በበኩላቸው በዛሬው ዕለት በደቡባዊ ሊባኖስ ማሮን አል ራስ በተሰኘ አከባቢ በእስራኤል ወታደሮች ላይ የቦምብ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከሊባኖስ ወደ ሰሜን እስራኤል የሚተኮሱ ሮኬቶች ተጠናክረው ቀጥለው ከትናንት ጀምሮ ከ240 በላይ ሮኬቶች መተኮሳቸው ተመላክቷል፡፡
በዛሬው ዕለት ብቻ 75 ሮኬቶች መተኮሳቸውንና አብዛኛዎቹ ኢላማቸውን ሳያሳኩ መምከናቸውን የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአውሮፓ ህብረት በሊባኖስ ለሰብዓዊ ቀውስ መከላከል ተጨማሪ 30 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ማድረጉን የህብረቱ ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን አስታውቀዋል፡፡