Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ መቀበል ወንጀል የተጠረጠሩ የአ/አ ገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች ላይ ለተጨማሪ ምርመራ 12 ቀን ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብር መጠን እንቀንሳለን በማለት ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ መቀበል ወንጀል የተጠረጠሩ የአ/አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች ላይ 12 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ለፖሊስ ተፈቀደ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቡድን ተጠርጣሪዎቹ በተጠረጠሩበት የጉቦ መቀበል ሙስና ወንጀል በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በመስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት አቅርቦ የተሰጣቸውን የስራ ኃላፊነትን ወደ ጎን በመተው ከግብር ከፋይ ግለሰቦች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ከግብር ከፋይ ድርጅቶች “ግብር እንቀንስላችኋለን” በማለት በመደራደር 100 ሚሊየን ብር የግብር መጠንን ወደ 13 ሚሊየን ብር ዝቅ በማድረግ ከተለያዩ ድርጅቶች፣ በተለያዩ መጠኖች ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ ተቀብለዋል በማለት የጥርጣሬ መነሻውን በመግለጽ የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ተፈቅዶለት እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበው በጊዜ ቀጠሮ ችሎት ጉዳያቸው የታዩት ተጠርጣሪዎቹ 1ኛ የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳዳር ገቢዎች ቢሮ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅ/ጽ/ቤት የታክስ ኦዲት ቡድን አስተባባሪ ሃብታሙ ግዲሳ፣ 2ኛ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች የታክስ ኦዲት ከፍተኛ ኦፊሰር ስምረት ገ/እግዚአብሔር፣ 3ኛ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች የታክስ ኦዲት ከፍተኛ ኦፊሰር ዮሴፍ ባቡ፣ 4ኛ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ታክስ ኦዲት ከፍተኛ ኦፊሰር አቤኔዘር ቶሎሳ፣ ከፍተኛ ግብር ከፋይ የታክስ ኦዲት ከፍተኛ ኦፊሰር ለሚ ሲሌ እና ገንዘብ ተቀባይ ባለሙያ ወ/ሮ መቅደስ አረጋዊ ናቸው።

የምርመራ ቡድኑ ከዚህ በፊት በተሰጠው 14 ቀናት ውስጥ ግለሰቦቹ ከተጠረጠሩበት ጉዳይ ጋር በተያያዘ የ7 ሰው የምስክርነት ቃል መቀበሉን፣ የተጠርጣሪዎችን የጣት አሻራ ማስነሳቱን፣ ተጠርጣሪዎች የሚጠቀሙበት የሞባይል ስልክ እና የኮምፒውተር ሀርድ ዲስክ ለምርመራ ለኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አገልግሎት መላክ፣ ተጠርጣሪዎች በሰጡት የባንክ የሂሳብ ቁጥር ገንዘቡ ከተላለፈላቸው ጋር ያላቸውን ዝምድና የማረጋገጥ ስራ መስራቱን ገልጿል።

ተጠርጣሪዎች ኦዲት ሲያደረጉት የነበሯቸውን የተለያዩ ድርጅቶች ላይ የተሰራውን የኦዲት ሪፖሪት ማምጣት፣ በከፊል የባንክ ማስረጃዎችን መሰብሰብ እና ቀደም ሲል በተጠርጣሪዎች የተሰራውን የታክስ ኦዲት እንዲሰራ የመጠየቅ ስራ መስራቱንም ጨምሮ ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስታውቋል።

የምርመራ ቡድኑ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አገልግሎት የተላከውን የተጠርጣሪዎች ሞባይል ስልክ ውጤት ማምጣትን ጨምሮ በርካታ ቀሪ የባንክ የሰነድ ማስረጃዎችን የማሰባሰብ እና መረጃውን የማስተንተን ስራ እንደሚቀረው ገልጿል።

በተለይም ገንዘብ በተለያዩ ባንኮች የተላለፈላቸውን የግንኙነት ጉዳይ ለመለየት እና በተጠርጣሪዎች ኦዲት የተሰራላቸው የድርጅት ባለቤቶችና ሰራተኞች ከሀገር ውጪ በስራ ምክንያት እና ለመስቀል በዓል ከአዲስ አበባ የወጡ መሆኑን ጠቅሶ ግለሰቦችን አስቀርቦ የምስክርነት ቃላቸው ለመቀበል እንዲሁም በተጠርጣሪዎች የተሰራውን የታክስ ኦዲት በገለልተኛ ባለሙያ ተሰርቶ ውጤቱ እስኪቀርብ ድረስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንደሚያስፈልገው የምርመራ ቡድኑ አብራርቷል።

ከዚህም በተጨማሪ በምርመራ ሂደት ላይ በርካታ አዳዲስ ግኝቶች ያገኘ መሆኑን በመጥቀስ በእነዚህ ላይ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በተገቢው የማሰባሰብ ስራ ለመስራት ከወንጀሉ ውስብስብነት ባህሪና ክብደት አንጻር ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ጉዳዩ በተጠናና በተደራጀ መልኩ በግብር ከፋዮች ላይ በሚሰሩት የታክስ አዲት ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠርና ደላላ በማዘጋጀት ለመንግስት የሚገባውን ታክስ ወደ ጎን በመተው ለግል ጥቅም የተፈጸመ የወንጀል ተግባር መሆኑን አመላክቷል።

የምርመራ ቡድኑ ተጠርጣሪዎቹ ካላቸው የገንዘብ አቅም፣ ከፈጠሩት ቡድን አንፃር እና በመንግስትና በህዝብ በላይ ያደረሱት ጉዳት ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር በዋስ ቢወጡ ማስረጃዎቻችንን ሊያጠፉ ወይም ምስክር ሊያባብሉብ እንደሚችሉ ግምቱን ጠቅሶ በወ/መ/ስ/ህ ቁጥር 59/2 መሰረት የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቀድለት ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች የፖሊስ የተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ አግባብ እንዳለ በመግለጽ ተከራክረው፤ የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲከበር ጠይቀዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ከቀሪ የምርመራ ስራ አንጻር ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ መፈቀድ እንዳለበት በማመን የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው በማለፍ የ12 ቀን የተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ ውጤቱን ለመጠባበቅ ለጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version