Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ልዩ ፍላጎት ላላቸው ሕጻናት አገልግሎት የሚሰጡ የበጎ አድራጎት ተቋማትን መደገፍ ይገባል – ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ልዩ ፍላጎት ላላቸው ሕጻናት እና ቤተሰቦቻቸው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የበጎ አድራጎት ተቋማትን መደገፍና ማጠናከር ይገባል ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ትኩረት ለሴቶችና ለህፃናት ማህበር ያስገነባውን ‘የግራር መንደር ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሕፃናት ማዕከል’ መርቀዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)÷ የህጻናት ጤናማና ደስተኛ እድገትን የሚፈታተኑ ችግሮች በመኖራቸው ተፈጥሮ የቸረቻቸውን ጣፋጭ የህይወት ሂደት በትክክል እንዳያጣጥሙ እንቅፋት ሲፈጥርባቸው ይስተዋላል ብለዋል፡፡

ሀገር ተረካቢ ሕፃናት በእውቀት፣ በመልካም ጤናና ሰብዕና ታንጸው እንዲያድጉ አስፈላጊው ቤተሰባዊ፣ ማህበራዊና ተቋማዊ ድጋፍና እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ተቋማቸው የሕፃናት መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ ብሎም በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት ለመለወጥ የሚያግዙ ንቅናቄዎችን እያካሄደ ይገኛል ብለዋል።

ማዕከሉ መገንባቱና ለአገልግሎት መብቃቱ ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።

ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታትና ለዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ማህበሩ እያደረገ ላለው ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ መግለጻቸውን የሴቶችና ህጻናት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ላለፋት 17 ዓመታት ከ12 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት ማከናወን እንደተቻለ የገለጹ ደግሞ ትኩረት ለሴቶችና ህፃናት ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ ሲስተር አሳየች ይርጋ ናቸው፡፡

Exit mobile version