Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኦሮሚያ ክልል በ6 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የእንስሳት መኖ እየለማ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በ6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የእንስሳት መኖ እየለማ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የመኖ ልማት ዳይሬክተር አቶ ሽብሩ ሆርዶፋ እንደገለፁት፥ በክልሉ የእንስሳት ሃብት ምርታማነትን ለማሳደግ ለመኖ ልማት ትኩረት ተሰጥቷል።

በዚህም አርሶ አደሮችን፣ አርብቶ አደሮችንና ባለሃብቶችን በማሳተፍ የእንስሳት መኖ እየለማ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ከ38 ሚሊየን ቶን በላይ መኖ መመረቱን አስታውሰው፤ ዘንድሮ 40 ነጥብ 8 ሚሊየን ቶን የእንስሳት መኖ ለማምረት መታቀዱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የሰብልና የግብርና ምርት እንዲሁም የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርት ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎችን በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች ተደራሽ በማድረግ የመኖ ምርቱን ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ከማህበራቱ ባሻገር የሳር ማጨጃና ማሰሪያ እንዲሁም የማቀነባበሪያ ማሽኖች ባሌ፣ ቦረና እና ጉጂ ዞኖች ለሚገኙ አርሶ እና አርብቶ አደሮች እየተሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።

የመኖ የዋጋ መናር በእንስሳት ተዋጽዖ ላይ የዋጋ ጭማሪ እያስከተለ መሆኑን አመልክተው፥ ችግሩን ለመቅረፍ በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ከ70 በላይ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በስራ ቢሆኑም ካለው ፍላጎት አንጻር መሸፈን የቻሉት 42 በመቶ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፤ አስተማማኝ የእንስሳት መኖ ልማት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የመኖ ዝርያ ከውጭ ጭምር በማስገባት ልማቱ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የክልሉ መስኖና አርብቶ አደር ቢሮ የኮንትራት ፕሮጀክቶችና መስኖ አስተዳደር አስተባባሪ አቶ ተመስገን ሩንዳ፤ ለቆላማ አካባቢዎች መኖ ልማት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ቆላማ ዞኖች የእንስሳት መኖ ልማት በመስኖና በመደበኛነት በ2 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ እየተካሄደ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

Exit mobile version