የሀገር ውስጥ ዜና

በጎንደር ከተማ ብልሹ አሰራርን መታገልና የአመራር ተጠያቂነትን ማስፋት ትኩረት ይፈልጋል ተባለ

By Shambel Mihret

October 03, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደር ከተማ ባለፈው አመት የነበሩ ወቅታዊ ችግሮችን በመቋቋም በርካታ ተግባራት ቢከናወኑም ብዙ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው የህዝብ ጥያቄዎች አለመመለሳቸውን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡

በከተማዋ የተጀመሩ መሰረተ ልማቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁና ህገወጥነትን በመከላከል በኩል ልዩ ትኩረት እንዲሰጥም ተጠይቋል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 12ኛ አመት 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ እናትነሽ ዋለ÷ ባለፈው በጀት አመት በብዙ ችግሮች ውስጥ ሆነን በርካታ ተግባራት ቢከናወኑም ሊመለሱ የሚገባቸው የህዝብ ጥያቄዎች አሁንም አሉ ብለዋል።

የተረጋጋ ሰላምና ፀጥታን በማረጋገጥ የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ አሰራሮችን ወደ ውጤት መቀየር ይገባል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ብልሹ አሰራርን በመታገል የአመራር ተጠያቂነትን ማስፋትም ሌላው ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመው÷ ለኑሮ ውድነቱ በቂ መፍትሄ ማበጀትና የከተማ ገቢን ለመሰብሰብ ጥረት ማድረግም ትኩረት የሚሻ ተግባር ነው ብለዋል።

የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው÷ ባለፈው አመት የተከናወኑ የሰላምና ፀጥታ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ጥረት መደረጉን በመግለጽ ጥፋተኞችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራም መሰራቱን ተናግረዋል።

ከመንግስት ቤቶችና የከተማ መሬት ቁጥጥርና አስተዳደር ጋር በተገናኘ ህገ ወጥ ተግባራት መበራከታቸውን ጠቅሰው÷ ይህንን ችግር ለመፍታትም ጥረት እንደተደረገ አስታውሰዋል።

በሙሉጌታ ደሴ