Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል አከባበር ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ በኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል አከባበር ወቅት የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶችን ይፋ አድርጓል፡፡

በርካታ ሕዝብ የሚታደምበት እና አባገዳዎች፣ ሀደ ስንቄዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የሚገኙበት የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል መስከረም 25 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይከበራል፡፡

በዓሉ በሠላም እንዲከበር የፀጥታ አካላት ትኩረት ሰጥተው ወደ ተግባር በመግባት እየሰሩ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡

በተለይም በዓሉ ወደሚከበርበት ስፍራ የሚመጡ ታዳሚዎች ለጋራ ደህንነት ሲባል ፍተሻ መኖሩን ተገንዝበው አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡

ከዚህ ቀደም የተከበሩ ኃይማኖታዊና ብሔራዊ በዓላት በሠላም እንዲከበሩ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር ወሳኝ ስራ ማከናወኑን ተመላክቷል፡፡

የዘንድሮው የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል በሠላም እንዲከበር የበዓሉ ታዳሚዎች እና የከተማው ነዋሪ የተለመደውን ትብብር እንዲያደርጉም ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በመሆኑም የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል ተከብሮ እስከሚጠናቀቅ ከመስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ጀምሮ በሚከተለው መሰረት መንገዶቹ ለተሽከርካሪ ለጊዜው ዝግ ይሆናሉ።

• ከቅዱስ ኡራኤል አደባባይ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ቅዱስ ኡራኤል አደባባይ ላይ

• ከቦሌ አቅጣጫ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ ተሽከርካሪዎች ኦሎምፒያ አደባባይ ላይና ታች እንዲሁም ግራና ቀኝ

• ከመስቀል ፍላወር ወደ ኦሎምፒያ የሚወስደው መንገድ ጋዜቦ አደባባይ ላይ

• ከአጎና ሲኒማ ወደ መስቀል አደባባይ ለከባድ ተሽከርካሪ አጎና ሲኒማ አጠገብ እንዲሁም ለቀላል ተሽከርካሪ ጥላሁን አደባባይ (አራተኛ ክፍለ ጦር ላይ)

• ከለገሀር መብራት ወደ መስቀል አደባባይ ለገሀር መብራት ላይ

• ከቴሌ ማቋረጫ ወደ ስታድዮም ለሚጓዙ ቴሌ ማቋረጫ

• ከራስ ሆቴል ወደ ስታድዮም ለሚመጡ ተሽከርካሪዎች ራስ ሆቴል ላይ

• ከሃራምቤ መብራት ወይም ከአምባሳደር ሲኒማ ወደ መስቀል አደባባይ ሃራምቤ መብራት ላይ

• ከብሔራዊ ቤተ መንግስት ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ብሔራዊ ቤተ መንግስት አጠገብ

• ከካዛንቺስ ሼል ወደ ባምቢስ የሚወስደው መንገድ ካዛንቺስ ሼል አጠገብ እንዲሁም

• ከጁፒተር ሆቴል ወደ ECA የሚወስደው መንገድ ባምቢስ ሳልኮት ህንፃ አጠገብ

በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ የሸገር ከተማ አካባቢዎች በርካታ ህዝብ በዓሉን ለማክበር ከዋዜማው ጀምሮ ወደ መዲናዋ የሚገባ በመሆኑ መላው ህብረተሰብ ተገቢውን አክብሮት በመስጠት የእንግዳ ተቀባይነት እሴቱን አጉልቶ ሊያሳይ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

በዓሉ በሚከበርበት ዙሪያ እና በአካባቢው በግራና በቀኝ ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ ፍፁም የተከለከለ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ህብረተሰቡ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት በ011-1-11-01-11 እንዲሁም በ991 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡

Exit mobile version