Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸምን ተከትሎ በባንኮች ያለው የውጭ ምንዛሬ ክምችት በ80 በመቶ ጨምሯል ተባለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 207 (ኤፍ ቢ ሲ) የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸምን ተከትሎ በባንኮች ያለው የውጭ ምንዛሬ ክምችት በ80 በመቶ ጨምሯል ሲሉ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ተናገሩ፡፡

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በዛሬው እለት ተገምግሟል፡፡

አቶ ማሞ ምህረቱ በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ አማካኝነት ላለፉት አምስት አስርት ዓመታት ስራ ላይ የቆየውን የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲ መሰረታዊ በሆነ መልኩ ማሻሻል ተችሏል ብለዋል፡፡

ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ትርጉም ባለው መልኩ እንዲቀረፍ ማድረጉን ነው የተናገሩት፡፡

ለአብነትም ማሻሻያውን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ወራት በባንኮችና በትይዩ ገበያ ያለውን የውጭ ምንዛሬ ልዩነት ወደ 3 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ መሰረት በባንክና ትይዩ ገበያ መካካል ያለው የውጭ ምንዛሬ ልዩነት ከመቶ በታች ከሆነ አፈጻጸሙ ጤናማ መሆኑንም አንስተዋል።

በሌላ በኩል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራውን ተከትሎ በወጪ ንግድ አፈጻጸም የተሻለ ስኬት መመዝገቡንም ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም በተያዘው መስከረም ወር የተመዘገበው የወጪ ንግድ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ53 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል፡፡

ከሃዋላ የተገኘው የወጪ ንግድ ገቢም ካለፈው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ145 በመቶ ብልጫ አለው ነው ያሉት፡፡

በከፍተኛ ሁኔታ ለኮንትሮባንድ ተጋልጦ የነበረው የወርቅ ወጪ ንግድም እጅግ መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከወርቅ ወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 58 ሚሊየን ዶላር ብቻ እንደነበር ጠቅሰው÷ በ2017 በጀት ዓመት እስከ አሁን ባለው ሂደት ከወርቅ ወጪ ንግድ 488 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡

ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸምን ተከትሎ በባንኮች ያለው የውጭ ምንዛሬ ክምችት በ80 በመቶ መጨመሩን ጠቁመው ይህም ማሻሻያው ስኬታማ አፈጻጸምን እያስመዘገበ መሆኑን ያሳያል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ስርዓቱን ጤናማነት ለመጠበቅ የጀመራቸውን ጥብቅ ቁጥጥሮች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

በዚህ ረገድ ብሔራዊ ባንክ ከውጭ ምንዛሬና ብድር አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ተገቢና ህጋዊ ያልሆነ አካሄድ በሚከተሉ ባንኮች ላይ ጠንካራ ቁጥጥርና የእርምት እርምጃ እንደሚወስድም አስገንዝበዋል፡፡

 

Exit mobile version