Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው የተሻለ አፈጻጸም አስመዝግቧል – አቶ አሕመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሁለት ወራት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገለጹ።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በዛሬው እለት ተገምግሟል፡፡

በመድረኩ የተገኙት አቶ አሕመድ÷ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ያለፉት ሁለት ወራት አፈጻጸም በዝርዝር መገምገሙን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በዚህም ማሻሻያው ኢኮኖሚው በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል ከማድረጉም ባሻገር በዜጎች ላይ የሚፈጠርን ማህበራዊ ጫና በቀነስ አግባብ መተግበሩን አንስተዋል፡፡

በቅርቡም የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ቡድን በማሻሻያው አፈጻጸም ላይ ግምገማ በማካሄድ በተሳካ መልኩ እየተተገበረ መሆኑን አረጋግጧል ብለዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዋነኛ ትኩረት የመንግስትን ገቢ ማሻሻል መሆኑን ጠቅሰው÷ በዚህም የሚኒስትሮች ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን አንስተዋል፡፡

በዚህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር የተሻለ ገቢ መገኘቱን ነው ያብራሩት፡፡

በቀጣይም የመንግስትን ገቢን የማሳደጉ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አቅጣጫ መቀመጡን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የገቢ ማሻሻያውን በሚመለከትም ከግብር ከፋዮች ጋር ሰፋ ያለ ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በዝቅተኛ ገቢ በሚተዳደሩ ዜጎች ላይ ጫና እንዳይፈጥር መንግስት አስቀድሞ የዝግጅት ስራ በማከናወን ወደ ትግበራ መግባቱንም ነው የገለጹት፡፡

በዚህም በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ዜጎች ከመስከረም ጀምሮ የሚተገበር የደሞዝ ጭማሪ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

መንግስት ዘይት በድጎማ እንዲገባ ማድረጉንና የማዳበሪያ ድጎማውም እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በከተማና ገጠር ለሚተገበር የማህበራዊ ሴፊቲኔት መርሐ- ግብርም መንግስት 60 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት በመያዝ ተጨማሪ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራው የእዳ ሽግሽግ ላይ የተሻለ ስራ መከናወኑን አንስተዋል፡፡

በዚህም ንግድ ባንክ ለተለያዩ የልማት ድርጅቶች አበድሮት የቆየውና ያልተከፈለን እዳ ለማሸጋሸግና ለካፒታል እድገት ጭማሪ በገንዘብ ሚኒስትር በኩል እስከ 900 ቢሊየን ብር የሚደርስ ቦንድ ለንግድ ባንክ ተሰጥቷል ነው ያሉት፡፡

በትሬዥሪ ቢል አማካኝነትም ለረዥም ጊዜ ያልተከፈሉ ብድሮች ወደ ረዥም ጊዜ ቦንድ እንዲቀየሩ መደረጉን ነው ያነሱት፡፡

የውጭ ሀገር የብድር ሽግሽግን በሚመለከትም በቡድን 20 የተቋቋመው የአበዳሪ ኮሚቴ ለኢትዮጵያ የብድር ማሸጋሸግ ዋስትና መስጠቱን ጠቅሰው÷ በቀጣይ ጥቂት ወራት ኢትዮጵያ የውጭ እዳ እፎይታ እንደምታገኝ ጠቁመዋል፡፡

ከልማት አጋሮች ጋር የሚደረገው ውይይትም ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል፡፡

Exit mobile version