ጤና

በአዳማ በ50 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የኦክስጂን ማምረቻ ፋብሪካ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

By Shambel Mihret

October 02, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በ50 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የኦክስጂን ማምረቻ ፋብሪካ ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ።

በዓለም ለ2ኛ ጊዜ እየተከበረ ያለው የዓለም የኦክስጂን ቀን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጤና ሚኒስቴር የሥራ ሀላፊዎች፣ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ሀላፊዎችና የጤና ባለሙያዎች በተገኙበት በአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ተከብሯል።

በዚሁ ወቅት በሆስፒታሉ በ50 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የኦክስጂን ማምረቻ ፋብሪካ ተመርቆ ለአገልግሎት መብቃቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በወቅቱ እንዳሉት÷ በሀገሪቷ የሚከሰቱ በርካታ ህመሞችን ለማከም በተለይም ለቀዶ ህክምና ኦክስጂን ወሳኝ ነው።

ለዚህም በሀገሪቷ ባሉ የጤና ተቋማት የኦክስጂን ማምረቻ ማዕከላትን በማስፋፋት አቅርቦትንና ጥራትን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኦክስጂን ማምረቻዎችን 45 ማድረስ መቻሉን ጠቁመው÷ ይህም በጤና ተቋማት በኦክስጂን እጥረት የተነሳ ህይወት እንዳይቀጠፍ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ስራ አስኪያጅ ዶክተር ስንታየሁ ታከለ በበኩላቸው የኦክስጂን ማምረቻ ማዕከሉ በሆስፒታሉ ህክምና አሰጣጥ ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።