Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢሬቻ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለው ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢሬቻ በዓል የሕዝቦችን ትስስር ለማጠናከርና የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተመላክቷል፡፡

የ2017 የኢሬቻ በዓል አከባበርን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ የባህል፣ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም ጋር ስትነጻጸር ብዙ የአደባባይ በዓላት እንዳላት ገልጸው÷ ይህም ከህብረ ብሔራዊ ብዝሃ ባህል ጸጋዎቿ የመነጨ ነው ብለዋል፡፡

የኢሬቻ በዓል በመስከረም ወር ከክረምት ወደ በጋ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገርን በማሰብ ለፈጣሪ ምስጋና ለማቅረብ የሚከበር የአደባባይ በዓል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዓሉ የሕዝቦችን ግንኙነት በማጠናከር እና እሴት እና ባህላቸውን እንዲለዋወጡ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ የቱሪስት ከተማ እየሆነች መምጣቷን ጠቁመው÷ ከተማዋን የቱሪስት መሸጋገሪያ ብቻ ሳይሆን መዳረሻ ለማድረግ የአደባባይ በዓላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢሬቻን መሰል የአደባባይ በዓላት የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው መጥቀሳቸውንም የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሚኤሳ ኤሌማ(ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የኢሬቻ በዓልን ለማክበር የተለያዩ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

Exit mobile version