አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የድሬዳዋ ፖሊስ አስተማማኝ ሰላም ማስፈኑ የድሬዳዋን የኢንዱስትሪና ንግድ ማዕከልነት ለማረጋገጥ ጉልህ ድርሻ ያበረክታል ሲሉ የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።
የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በስራ አፈፃፀማቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ አመራርና አባላቱ ዕውቅናና ሽልማት አበርክቷል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የአስተዳደሩ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፈትህያ አደንን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
ከንቲባ ከድር ጁሃር በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ፖሊስ አሠራሩንና አደረጃጀቱን አስተካክሎና ከህብረተሰቡ ጋር ተሳስሮ አስተማማኝ ሰላም እና ፀጥታ እንዲረጋገጥ ተግቷል።
በተለይም በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ የወንጀል መከላከልና የፀጥታ ማረጋገጥ ስራዎች በማከናወን ረገድ የድሬዳዋ ፖሊስ አበረታች ተግባር መፈጸሙን ገልጸዋል።
እነዚህ አበረታች ተግባራት ድሬዳዋን የምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከልነት እንዲረጋገጥ ማገዛቸውን ማስታወሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የተዘጋጀው የዕውቅናና የሽልማት መርሃ-ግብር ፖሊስ ተልዕኮውን በተሻለ እንዲፈጽም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ከንቲባው ተናግረዋል፡፡