የሀገር ውስጥ ዜና

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቡና ተከል ሽፋን ከ228 ሺህ ሄክታር በላይ መሆኑ ተገለጸ

By Meseret Awoke

October 02, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ228 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በቡና እየለማ እንደሚገኝ የክልሉ ግብርና ቢሮ የቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በ2016 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና በ2017 ዕቅድ ዙሪያ በወላይታ ሶዶ ከተማ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው፡፡

በክልሉ ግብርና ቢሮ የቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዳይሬክተር ተወካይ አቶ አማኑኤል ብሩ፤ በክልሉ ለቡና ልማት ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም በክልሉ ከ228 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በቡና እንዲሁም ከ71 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ደግሞ በቅመማ ቅመም ሰብል ተሸፍኖ እየለማ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ምርታማነትን ለማሳደግ በ7 ሺህ 204 ሄክታር ማሳ ላይ አዲስ የቡና ችግኝ እና 3 ሺህ 800 ሄክታር ማሳ ላይ ያረጀ ቡናን በመንቀል በአዲስ የመተካት ስራ መከናወኑንም አመላክተዋል።

በክልሉ የሚገኙ የቡና አምራች አርሶ አደሮች ተጠቃሚነት እያደገ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ይህን ለማሳደግ ቡናን ከማስፋት ባሻገር በጥራት የማምረት ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ከቅመማ ቅመም ልማት አንፃርም፥ ክልሉ ሰፊ ፀጋዎች ያሉት ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ምርት እየተገኘ ባለመሆኑ ለዘርፉ አፅንኦት መስጠት እንደሚገባ መጠቆማቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመልክቷል።

በመድረኩ የዞንና የወረዳ ቡናና ቅመማ ቅመም ጽ/ ቤት ኃላፊዎች፣ ቡድን መሪዎች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።